ዓለምአቀፋዊ ዜና

ግማሽ ያኅሉ የአውስትራሊያ ምርጥ አትሌቶች “ከድኅነት ወለል በታች” ይኖራሉ – ጥናት

By Alemayehu Geremew

August 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግማሽ ያኅሉ የአውስትራሊያ ምርጥ አትሌቶች “ከድኅነት ወለል በታች” እንደሚኖሩ የአውስትራሊያ ስፖርቶች ፋውዴሽን ጥናት አመላከተ፡፡

የሚያገኙት ዓመታዊ ገቢም አውስትራሊያ በደረጃዋ “ከድኅነት ወለል በታች” ብላ ከምትመድበው የ23 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር ወይም የ15 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የገቢ እርከን በታች መሆኑን ፋርስ ኒውስ አስነብቧል፡፡

ዛሬ ይፋ የሆነው የፋውንዴሽኑ ጥናት ውጤት እንዳመላከተው÷ አውስትራሊያ በጊዜ ብሔራዊ ጀግኖቿን እቅፍ ድግፍ ማድረግ ካልጀመረች ከዋና ዋና ዓለም አቀፋዊ የስፖርታዊ ውድድር መድረኮች የምትሰወርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

እንዲያውም አሶሼትድ ፕሬስ ቀደም ብሎ እንዳወጣው መረጃ አውስትራሊያ ለአትሌቶቿ ትኩረት መሥጠት ካልጀመረች ቀላል ቁጥር ነው የማይባል አትሌት ሊኮበልልባት ይችላል ማለቱንም ፋርስ አስታውሷል፡፡

ጥናቱን የሠራው የአውስትራሊያ ስፖርቶች ፋውዴሽን ሰበሰብኩ ባለው አኀዛዊ መረጃ ከ2 ሺህ 304 አውስትራሊያዊ አትሌቶች መካከል 600 ያኅሉ በ60 የስፖርት መስኮች በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉ ናቸው፡፡

በሰጡት አስተያየትም በዓለምአቀፍ መድረክ ለመወዳደር፣ የተለያዩ የስፖርት ትጥቆችን ለመግዛት፣ ለጉዞ እንዲሁም በሚወዳደሩበት ሀገር ለመቆየት እና አልጋ ለመያዝ የሚወጡ ወጪዎች ጫና እንደሚያሳድሩባቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አትሌቶቹ ስፖርታዊ ጨዋነታቸውን እና ብሔራዊ ክብራቸውን ጠብቀው በመድረኩ ገቢ ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል።

ዕድሜያቸው ከ18 – 34 ባለው ገደብ ውስጥ ከሚገኙ ሦስት አትሌቶች መካከል ሁለቱ አትሌቲክስን ለማቆም እንዳሰቡም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

እንደ ጥናቱ ከሆነ አሁን ላይ ከ40 በመቶ በላይ አትሌቶች ከባለፈው ዓመት በከፋ ጥልቅ ድኅነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡