የሀገር ውስጥ ዜና

ከ21 ኪ.ግ በላይ አደንዛዥ ዕጽ ተያዘ

By Amele Demsew

August 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ21 ኪ.ግ በላይ አደንዛዥ ዕጽ መያዙን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ ፡፡

በበረራ ቁጥር ኢቲ-913 መነሻውን ካሜሮን አድርጎ አዲስ አበባ የገባው አደንዛዥ ዕጹ በበረራ ቁጥር ኢቲ-901 ከአዲስ አበባ ወደ ናይጀሪያ ሊወጣ ሲል በአየር መንገዱ የደህንነት ክትትል ሰዎች መያዙ ተገልጿል፡፡

መጠኑ 21.7 ኪሎግራም የሆነው ይህ አደንዛዥ ዕጽ ኮኬይን በመባል የሚታወቀው የአደንዛዥ ዕጽ ዓይነት መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

በሻንጣ ተደብቆ ወደሀገር የገባውና ከሀገር ሊወጣ ሲል የተያዘው አደንዛዥ ዕጽ ማለፍ ቢችል በተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበርም መግለጫው አመላክቷል፡፡

በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ የፍተሻ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ኤርፖርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በቅንጅት ባደረጉት ጠንካራ ፍተሻና ጥብቅ ቁጥጥር የተያዘውን አደንዛዥ ዕጽ ሲያዘዋውር የተገኘው የናይጀሪያ ዜግነት ያለው ግለሰብ ነው፡፡

በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በህግ ቁጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ ናይጀሪያዊ ግለሰብ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል፡፡

በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዋና መምሪያ ከአጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት የመንገደኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!