የሀገር ውስጥ ዜና

ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተከናወኑ ስራዎች ውጤት ተመዝግቧል – አቶ ብናልፍ አንዷለም

By Amele Demsew

August 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላምን ለማስፈን በተከናወኑ ሥራዎች የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም እንደገለጹት ÷ እንደሀገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና በማህበረሰቡ ውስጥ የሰላም ግንባታን ለማጠናከር በተከናወኑ ስራዎች ውጤት ተመዝግቧል።

ህዝብና መንግስት ተቀናጅተው ባከናወኗቸው ሥራዎች የሰላም እጦት በነበረባቸው አካባቢዎች ጭምር ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን በማሳያነት አንስተዋል።

በየጊዜው የተካሄዱ የሰላም ምክክሮች፣ የገፅታ ግንባታ ሥራዎች እንዲሁም ሰላምን የሚያጎለብቱ መልካም እሴቶችን ለማስፋት የተደረገው ጥረት የሰላም ባህል እንዲገነባ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተለይ በአንዳንድ ክልሎች በተከናወኑ ጠንካራ የሰላም ግንባታ ሥራዎች በህዝቦች መካከል የተሻለ አንድነትና ሰላም እንዲጎለብት ለማድረግ ተችሏል ሲሉም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በቀጣይም በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ክልሎች የተቀናጀ ሥራ ማከናወን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው ÷ መንግስት የዜጎችን ሰላም የማረጋገጥና የህግ የበላይነትን የማስፈን ሥራዎችን በተጠናከረ መንገድ ይሰራሉ ብለዋል፡፡

በተለይ የክልሎች እና የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጎልበት ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡