የሀገር ውስጥ ዜና

የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Amele Demsew

August 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኔትዎርክ ስርጭት የሚያገለግሉ ፓወር ባትሪዎችን የሰረቁ የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች እና በወንጀሉ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ሌሎች ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የስርቆት ወንጀሉ የተፈፀመው በየካ ክ/ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ በቀን ስራ ተቀጥሮ የሚያገለግል የጥገና ባለሙያ እና በኤጀንሲ የተቀጠረ አሽከርካሪ ተቋሙ በተለያዩ ቦታዎች ከተከላቸው የኔትዎርክ ሳጥኖች ውስጥ ለኔትዎርክ ስርጭት የሚያገለግሉ 11 ፓወር ባትሪዎችን መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡

ከተቋሙ በተሰጠ ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ተገቢውን ክትትል በማድረግ የወንጀሉን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር ሊውሉ እንደቻሉ ነው የተገለጸው፡፡

የተሰረቁት ንብረቶችም ከተሸጡበት እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን እነዚህን ንብረቶች የገዙ ሁለት ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በኪራይ የሚገለገልበት እና ንብረቶቹ የተጫኑበት ተሽከርካሪም ተይዟል።