የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

By Amele Demsew

August 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፤ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ያቀረቡትን የመልቀቂያ ጥያቄ የተቀበለው ምክር ቤቱ በምትካቸው አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በማድረግ መሾሙን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አረጋም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

አቶ አረጋ ከበደ ባለፉት ጊዜያት የክልሉን ስራና ስልጠና ቢሮ ሲመሩ የቆዩ ሲሆን ከዚያ በፊትም በተለያዩ ተቋማት በሃላፊነት ሲሰሩ ቆይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ÷ ክልሉ አሁን ካለበት ዘርፈ ብዙ ችግር ወጥቶ የተሻለ እና የተረጋጋ ክልል እንዲሆን ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በጦርነት እና ውስብስብ ችግሮች ውስጥ በክልሉ ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮችን ያሳዩን የቀድሞ መሪዎች ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ክልሉ ፥ የምጣኔ ሃብት፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ችግሮች ያሉበት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መሥተዳድሩ ያጋጠመንን ውስብስብ ችግር ለመውጣት የአባቶቻችንን ብስለትና የሕዝባችንን ስክነት እንደመውጫ መፍትሔ እንጠቀማለን ነው ብለዋል፡፡