Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአክሱም ሃውልትና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአክሱም ሃውልትና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ታሪካዊ ይዘታቸው ተጠብቆ ለመጠገን የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም ቅርሶች ያሉበትን ደረጃ ለመለየት አስቸኳይ የዳሰሳ ጥናት መካሄዱንም ባለስልጣኑ ገልጿል።

ከእነዚህ ታሪካዊ ስፍራዎችና ቅርሶች መካከል የአክሱም ሃውልትና የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት እንደሚገኙበት በባለስልጣኑ የቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ አብረሃ ገልጸዋል።

በአክሱም በተካሄደው ጥናት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት በአካባቢው ያለው ታሪካዊው ሃውልት ወደ አንድ አቅጣጫ የመዝመም ሁኔታ እንደተስተዋለበት መመልከቱን አስረድተዋል።

ከዚህ የተነሳም 31 ሜትር ቁመት ያለውና ወደ ሰሜን አቅጣጫ የዘመመው የአክሱም ሃወልት ከአራት ዓመታት በፊት በ115 ሚሊየን ብር በጀት ለመጠገን የፌዴራል መንግስት ከአንድ የጣሊያን ተቋራጭ ጋር ውል መግባቱን አስታውሰዋል።

በውሉ መሰረት ተቋራጩ ለጥገና የሚያስፈልጉ ዕቃዎች መጓጓዝ በጀመረበት ወቅት በኮሮናና በጦርነት ምክንያት እንደተቋረጠ አስታውሰዋል፡፡

አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ውሉን በማደስ የጥገና ስራ በተያዘው በጀት ዓመት ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ከአለት ተፈልፍሎ የተሰራው ታሪካዊው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ማደስ የሚያስችል ከቀድሞ በተጨማሪ የባለሙያዎች ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈረንሳይ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት የተገኘው የፋይናንስ ድጋፍ አጠናክረን የላሊበላን ታሪካዊ ቅርስ የነበረ ይዘቱን ጠብቆ የማደሱ ተግባር እንዲቀጥል እተሰራን ነው ብለዋል።

የአክሱም ሃወልትና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጥናት ለማጠናከርና ለመጠገን የሚደረገውን የተቀናጀ እንቅስቃሴ ለማሳካት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

Exit mobile version