አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ በጎ አድራጎት ድርጅት በ130 ሚሊየን ብር በመቱ ከተማ ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠ፡፡
በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የክልል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ማኅተመ በቃሉ እንደገለጹት÷ በመቱ ከተማ በሚገኘው የድርጅቱ ቅርንጫፍ ለ50 አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው።
ድርጅቱ የሚያስገነባው ማዕከል ከኢሉ አባቦር በዞኑና አጎራባች ክልሎች የሚገኙ ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንንና የአዕምሮ ሕሙማንን ለመንከባከብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም የመንግስት አካላት የማዕከሉን ግንባታ እንዲያግዙና የበጎ አድራጎት ስራውን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።
የመቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግርማ ታረቀኝ÷ ከተማ አስተዳደሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን በቅርበት ያግዛል ብለዋል።
የኢሉ አባቦር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው÷ የበጎ አድራጎት ተግባር ከመልካም ልብ የሚመነጭ በመሆኑ ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የመቱ ከተማ ነዋሪዎችም ከበጎ አድርጎት ድርጅቱ ጎን በመሆን የተቸገሩትን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።