የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ተካሄደ

By Amele Demsew

August 19, 2023

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ወግ የውይይት መድረክ “የክረምት ትጋት የዓመት ልማት” በሚል ርዕስ

ተካሂዷል፡፡

ተወያዮቹም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምጸሐይ ጳውሎስ፣ የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር)፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድና የደጃዝማች ወንድይራድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ር/መምህር ሰለሞን ክቤ ናቸው፡፡

ዓለምጸሐይ ጳውሎስ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕዝቡ ተሳትፎ በክረምቱ በሁሉም ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ለበጋው መሰረት የጣሉ እና ጽናትን ያየንባቸው ናቸው ብለዋል ።

ከ20 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በክረምቱ በበጎ ፈቃድ ስራ ተሰማርተው ማህበረሰቡን እንዳገለገሉ ጠቅሰው÷ የሌማት ትሩፋትም የሁሉም ቤተሰብ ስራ እየሆነ ይገኛል ነው ያሉት።

አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ግማሽ ያህሉ የቆዳ ስፋት የተለያየ አይነት የመሬት መጎዳት እንደገጠመው አስረድተዋል፡፡

በአንድ ዓመት ብቻ በአፈር መከላት ምክንያት ኢትዮጵያ 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ሃብት እንደምታጣ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ አንስተዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም የምርትና ምርታማነት፣ ዘላቂ የልማት ግቦች፣ የስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የደን ሽፋን ጥያቄዎቻችንን በጋራ ለመመለስ ጅምር ሆኖናል ብለዋል።