አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋና ላምሮት የድምፃውያን የተሰጥዖ ውድድር የምዕራፍ 14 የፍፃሜ ውድድር ነገ ይካሄዳል፡፡
ከ2011 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ መድረክ ያጡ ድምፃውያንን መድረክ እንዲያገኙ ያስቻለው ፋና ላምሮት በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን እያሳየ ቀጥሏል።
ፋና ላምሮት በአመት ውስጥ የአሸናፊዎች አሸናፊን ጨምሮ አራት ምዕራፎችን የሚያካሂድ ሲሆን÷ እያንዳንዱ ምዕራፍ ለዘጠኝ ሳምንታት ይቆያል።
በሶስት የተለያዩ ምዕራፎች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ላይ አንድ ላይ ይገናኛሉ።
አሁን ፋና ላምሮት 14ኛው ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን÷ ጠንካራ ተፎካካሪዎችን ላሳየን የምዕራፍ 14 ውድድር የ1 ሚልየን ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል።
1 ሚልየን ብሩን ተወዳዳሪዎች እንደየደረጃቸው ይካፈላሉ።
ላለፉት 8 ሳምንታት በዳኞችና በራሳቸው ምርጫ ሲወዳደሩ የነበሩ ተወዳዳሪዎች በነገው የፍጻሜ ውድድር ላይ ትንሳኤ ስለሺ፣ ትግስት አስማረ፣ አፀደማርያም ያረጋል እና ባምላክ ቢያድግልኝ ከኮከብ ባንድ ጋር በ3 ዙር ሙዚቃቸውን በማቅረብ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ነገ ቅዳሜ ከ6:00 ሰአት ጀምሮ የምዕራፍ 14 የፍፃሜ ውድድርን ራዲዮን ጨምሮ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች በቀጥታ ስርጭት እየተመለከታችሁ በ8222 ላይ በእለቱ የሚገለፀውን የኮድ ቁጥር በመላክ መደገፍ እና መዝናናት ትችላላችሁ።