የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ፓርቲዎች ከምርጫ ጋር ተያይዞ እየተነሱ ላሉ ችግሮች ኢ-ህገመንግስታዊ መፍትሔዎችን እንደማይቀበሉ ገለፁ

By Tibebu Kebede

May 08, 2020

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 30፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፓርቲ ወይም ከቡድን ፍላጎት በመውጣት የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ እና ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን አስታወቁ።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)፣ የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (የተኦነግ) እና የኦሮሞ ሃርነት ፓርቲ (ኦአፓ) በሃገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ኮቪድ-19፣ በህዳሴ ግድብ ምክንያት የሉዓላዊነት አደጋ፣ በኮቪድ እና በሌሎች ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል የኢኮኖሚ ድቀት እና በያዝነው ዓመት ሊከናወን የነበረው ምርጫ 2012 ጋር የተያያዙ ፈተናዎች ሀገሪቱ ላይ መደቀናቸውን ነው ያስታወቁት።

እነዚህ ችግሮች የተባበረ አቅም የሚጠይቁ መሆናቸውን ያነሱት ፓርቲዎቹ፥ ከፓርቲና ከቡድን ፍላጎት በመውጣት የሃገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍና ሃገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም መንግስት የጋራ ስራዎችን አቀናጅቶ በመምራት የሚጠበቅበትን ህጋዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

እኛ በኦሮሚያ ክልል የምንቀሳቀስ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ፣ የኦሮሞ አንድነት ነፃነት ግንባር (ኦአነግ) ፣ የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (የተኦነግ) እና የኦሮሞ ሀርነት ፓርቲ (ኦአፓ) ዛሬ ሚያዚያ 30/2012 በሀገራችን እና በክልላችን ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል።

በውይይታችንም አራት ከባባድ ችግሮች በአንድ ጊዜ አገራችን ላይ መደቀናቸውን አይተናል።

እነሱም ኮቪድ-19፥ በህዳሴ ግድብ ምክንያት የተደቀነ የሉአላዊነት አደጋ፥ በኮቪድ እና በሌሎች ምክንያቶች ሊከሰት የሚችለዉ የኢኮኖሚ ድቀት እና በያዝነዉ ዓመት ሊከናወን የነበረዉ ምርጫ 2012 ናቸዉ።

እነዚህ ችግሮች ተደራርበዉ ይቅርና በተናጥልም የተባበረ አቅም የሚጠይቁ መሆናቸዉ አያጠያይቅም።

ስለሆነም ከፓርቲ ወይም ከቡድን ፍላጎት በመዉጣት የሀገሪቱን ችግሮች ለመቅረፍ እና ሀገራዊ ለዉጡን ለማስቀጠል አብሮ ተባብሮ መስራት እጅግ ወሳኝ መሆኑን እና መንግስት ደግሞ የጋራ ስራዎችን አቀናጅቶ በመምራት የሚጠበቅበትን ህጋዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ተስማምተናል።

በዛሬ ዕለት በሀገራችን አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በጥልቀት እና በዝርዝር ከተወያየን በኋላ ባለሦስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥተናል።

  1. የህዝብ ህይወት እና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ከየትኛዉም የፖለቲካ አጀንዳ በላይ ነዉ።

በኮሮና ምክንያት የህዝባችን ጤንነት እና ህይወት ለከፍተኛ አደጋ በተጋለጠበት፥ በህዳሴ ግድብ ዉሃ ሙሌት ምክንያት የሀገራችን ሉአላዊነት ስጋት ላይ ባለበት እና በኮሮናና በሌሎች ምክንያቶች በኢኮኖሚያችን ላይ ከፍተኛ የድቀት አደጋ በተጋረጠበት በአሁኑ ወቅት ልዩነቶችን አቻችሎ በአንድነት መቆም ሲገባ ትናንሽ አጀንዳዎችን በመፍጠር ህዝቡ ራሱንና ሀገሩን ለማዳን እንዳይረባረብ ማድረግ ከክህደቶች ሁሉ በላይ ክህደት ነዉ።

እኛ በኦሮሚያ ክልል የምንቀሳቀስ ፓርቲዎች በዚህ ወሳኝ ወቅት የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ወደጎን በማድረግ የህዝባችንና የሀገራችንን ህልውና ለመታደግ በጋራ ለመስራት ወስነናል።

  1. በየትኛዉም አለም የትኛዉም ችግር በምርጫ አይከሰትም። ለሚደርሱብን ችግሮች ግን መፍትሔዎችን መምረጥ እንችላለን።

በአሁኑ ወቅት ካለንበት ሁኔታ እና ከተጀመረዉ ሀገራዊ ለውጥ አንፃር በየትኛዉም ደረጃ ለሚፈጠሩ ችግሮች የሚሰጡ መፍትሔዎች ፍፁም ህጋዊ እና ህገ-መንግስታዊ መሆን አለባቸዉ።

ስለሆነም እኛ በኦሮሚያ ክልል የምንቀሳቀስ ፓርቲዎች ከምርጫ ጋር ተያይዞ እየተነሱ ላሉት ችግሮች ኢ-ህገመንግስታዊ መፍትሔዎችን የማንቀበል መሆናችንን እናረጋግጣለን።

  1. በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ላይ ከተደቀኑ ተደራራቢ እና አስቸጋራ ጫናዎች አንፃር ጠንካራ መንግስት ያስፈልጋል።

በሽግግር ስም ዓለማቸዉ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ፓርቲዎችን የሚያካትት መንግስት በየትኛዉም መስፈርት ጠንካራ ሊሆን አይችልም።

ኮቪድ-19 በአለምና በሀገራችን ከፍተኛ ስጋት በደቀነበት ምርጫ ማካሄድ ቀርቶ ማሰቡም ለህዝብ ህይወት ደንታቢስነት ነዉ።

እኛ የኦሮሚያ ክልል ፓርቲዎች በስልጣን ጥማት የተነሳ በሽግግር መንግስት ወይም በምርጫ ስም ህዝብንና መንግስትን ለማወናበድ የሚደረገዉን ሩጫ በጥብቅ የምናወግዝ መሆናችንን እናሳዉቃለን!