ጤና

የህፃናት ቶንሲል ህመምና መፍትሔው

By Amele Demsew

August 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቶንሲል ህመም በትንፋሽ የሚተላለፍ በሕጻናት ላይ በስፋት የሚከሰት የጉሮሮ ህመም አይነት ቢሆንም በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች ላይ ሲከሰት ይችላል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህጻናት ህክምና ስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ፋሲል መንበረ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት÷ የቶንሲል ህመም (tonsilitis) ዋና ዋና ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው፡፡

እነሱም፦ በቫይረስ የሚመጣና በባክቴሪያ የሚመጣ ተብለው የሚከፈሉ ሲሆን በቫይረስም ሆነ በባክቴሪያ የሚከሰት የቶንሲል ህመም በማስነጠስና በማሳል ወይም በየትኛውም አመቺ ሰዓት ከአፍና ከአፍንጫ ከሚወጡ ፈሳሽ ነገሮች በሚደረግ ንክኪ እንደሚተላለፉ ይገልጻሉ፡፡

የቶንሲል ህመም በምን ምክንያት እንደተከሰተ በትክክል ለመለየት የሚችሉት የጤና ባለሙያዎች በሚያደርጉት ምርመራ ሲሆን በህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም ቢታዩ የተሻለ ነው ይላሉ ዶክተር ፋሲል::

ከባክቴሪያ የሚመጣው የቶንሲል ህመም በወቅቱ ካልታከመ የልብ እና የኩላሊት ህመሞችን ሊያከስትል እንደሚችል ነው የሚናገሩት ባለሙያው፡፡

የቶንሲል ህመምና ጉንፋን በህጻናት ላይ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት የሚገልጹት ዶክተር ፋሲል፤ ለዚህም ምክንያቱ ህፃናት አዲስ ፍጥረት በመሆናቸው ደማቸው ገና ብዙ አይነት ቫይረሶችና ባክቴሪያዎችን ተለማምዶ የራሱ የሆነ ተዋጊ ነጭ የደም ሴሎች እና ኬሚካሎችን እስኪያመርት ድረስ ጊዜ ስለሚያስፈልገው ነው ይላሉ፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ ህፃናት ከአዋቂዎች ይልቅ እርስ በርስ በጣም ስለሚቀራረቡ እና ስለሚነካኩ በቀላሉ በህመሙ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም ÷ በተለያዩ ምክንያቶች የክብደት መቀነስ የሚታይባቸውና የምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናት በሽታ የመከላከል አቅማቸው ዝቅተኛ ስለሆነ በተደጋጋሚ የቶንሲል ህመም ሊይዛቸው እንደሚችል ያነሳሉ፡፡

አንዳንድ ህፃናት ደግሞ በተፈጥሯቸው ወይም በተደጋጋሚ ኢንፌክሽን ምክንያት የቶንሲል እብጠቶች ሊከሰትባቸው የሚችሉ ሲሆን እብጠቱ በቫይረስም ሆነ በባክቴሪያ በቀላሉ ሲቆጣ እና ከነበረበት እብጠት የበለጠ ተባብሶ የጉሮሮ ህመም እና ማንኮራፋት ሊያስከትልም ይችላል ይላሉ ዶክተር ፋሲል::

እንደዚህ አይነት ችግር ላለባቸው ህጻናት የጤና ባለሙያዎች ቀዶ ጥገና በማድረግ ለህመሙ ፈውስ ሊያስገኙ የሚችሉበት አማራጭ እንዳለም ነው የሚናገሩት፡፡

የቶንሲል ህመም የሚከተሉትን ምልክቶች ህፃናት ላይ የሚያሳይ ሲሆን እነዚህም ፦ ትኩሳት፣ ለመዋጥ መቸገር፣ የጉሮሮ ህመም ፣ ራስ ምታት ፣ የአፍ መጥፎ ሽታ፣ የቶንሲል ማበጥ እና መቅላት፣ የእንጥል እና ጉሮሮ መቅላት፣ ቶንሲል ላይ የሚታይ ነጭ ወይም ቢጫ ሽፋን፣ የአንገት አካባቢ ንፍፊት/እብጠትና ማንኮራፋት እንደሆኑ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ምልክቶች ከ2 እስከ 4 ቀናት ሊቆዩ እንደሚችሉና ጠንከር ካለም እስከ 2 ሳምንት ሊቆይ ይችላል ይላሉ፡፡

ቶንሲል በቤት ዉስጥ በሚደረጉ ህክምናዎች መፈወስ የሚቻል ሲሆን ከነዚህም መካከል፦ የዝንጅብል ሻይ መጠቀም፣ ሙቅ ዉሃ ዉስጥ ጨው በማድረግ ጉሮሮ ላይ መያዝ ወይም ጉሮሮን ማጠብ ወይም መጉመጥመጥ ፣ በተደጋጋሚ ትኩስ ፈሳሽ ነገሮችን መውሰድ፣ በቂ እረፍት ማድረግ፣ ሻይ በማር መጠጣት፣ ነጭ ሽንኩርት መጠቀም ፣ የውሃ እንፋሎት መታጠን፣ የብርቱካን ወይም ሎሚ ጭማቂ መውሰድን ባለሙያው ይመክራሉ፡፡

በተጨማሪም ÷ ቀለል ያሉ የህመም ማስታገሻዎች መውሰድ፣ ለምሳሌ ፓራሴታሞል ፣ ጠንካራ እና ጉሮሮ ሊረብሹ የሚችሉ ምግቦችን ማስወገድ የሚሉትን ይጠቅሳሉ፡፡

ሆኖም ግን ህመሙ ከፍተኛ ከሆነ፣ ቶንሲል ላይ ነጭ ሽፋን ካሳየ፣ በቤት ውስጥ ሕክምና ቢያንስ በሁለት ቀን ለውጥ ከሌለው፣ ማንኮራፋት እና እንቅልፍ መንሳት ካለ፣ ምግብ ሙሉ ለሙሉ መዋጥ ካልተቻለና የታወቀ የልብ ህመም ካለ በቤት ውስጥ ሕክምና ሊድን ስለማይችል በጤና ባለሙያ መታየት ያስፈልጋል ይላሉ ዶክተር ፋሲል፡፡

ለህፃናት ጠንካራ የህመም ማስታገሻዎችን ለምሳሌ አስፕሪን እና የመሳሰሉት መጠቀም አይመከርም::

በተጨማሪም ፀረ ባክቴርያ መድሃኒቶች ለምሳሌ አሞክሳሲሊን፣ አዚትሮማይሲን እና የመሳሰሉትን ያለ ሀኪም ትእዛዝ መጠቀም በማህበረሰባችን ውስጥ መድሃኒት የተለመዱ ባክቴርያዎች እንዲበዙ ያደርጋል ይህ ደሞ ሕክምናውን አስቸጋሪ ያደርገዋል ::

ስለዚህ ፀረ ባክቴርያ መድሃኒቶች ለህፃናትም ሆነ ለአዋቂዎች ያለ ሀኪም ትእዛዝ መጠቀም በፍፁም አይመከርም ::

ጨቅላ ህፃናትም ሆነ ታዳጊ ህፃናት የህመም ምልክት ካሳዩ በቀጥታ የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም ጋር መሄድ እና ማሳየት እንደሚያስፈልግም ያሳስባሉ፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው