ፋና ስብስብ

በጽኑ ህመም ውስጥ ከነበረች ልጃቸው ጎን ለ38 ዓመታት ያልተለዩ እናት

By Meseret Awoke

August 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እናት ከራሷ ደስታ እና ጊዜ በላይ ለልጇ የምትሰጠው እንዳይጎድልባት ዋጋ የምትከፍል ናት፡፡

‘ጎሽ ለልጇ ስትል በጦር ተወጋች’ እንዲሉ እናት የልጇን ህይወት ከእርሷ አስበልጣ እስከሞት ዋጋ ትከፍላለች።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እናት ለልጆቿ ስትል የምትከፍለው መስዕዋትንት ከቃላት በላይ እንደሆነ እንመለከታለን፤ ከሰሞኑም በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የሰፈረው የእናትና ልጅ ታሪክ ይህን እውነታ ያሳያል።

ኤድዋርዳ ኦባራ የተባለች የስኳር ህመምተኛ አሜሪካዊት ታዳጊ በ16 ዓመቷ በፈረንጆቹ 1969 የሳንባ ምች ሰለባ ስትሆን በሽታው ተደራራቢ እና ጽኑ ስለሆነም ቤተሰብ ወደሆስፒታል ቢወስዷት ሊሻላት አልቻለችም፡፡

በዚህ ጭንቅ ውስጥ ልጅ የእናቷን አይን እያየች ‘’እናቴ ከጎኔ አትለይ’’ ስትል ትጠይቃለች፡፡ እንኳን አደራ ተብላ እንደውም የእናት አንጀት እንስፍስፍ ነውና በፍጹም ከጎንሽ አልለይም በማለት እናት ለልጃቸው ቃል ገቡ።

ኤድዋርዳ ህመሟ ይጸናባትና በጽኑ ህመም (ኮማ) ውስጥ ሆና ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት ተቆጠሩ፤ ዓመታትም አልፈው አደዋርዳ ከገባችበት ጽኑ ህመም ውስጥ ሳትወጣ ለ42 ዓመታት ቆይታ ህይወቷ አለፈ።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥም እናት ልጃቸውን ከተኛችበት አልጋ ሳይርቁ የሚችሉትን ሁሉ እንክብካቤ አደረጉ። እንቅልፍ ከ90 ደቂቃ በላይ ተኝተው የማያውቁት እናት ለልጃቸው ሙዚቃ በማንጎራጎር፣ መጽሃፍት በማንበብ እና ታሪኮችን በመንገር ያሳልፉ ነበር።

ቤተሰቡን ይደጉም የነበረው አባትም ልጁን መንከባከብ ግድ ሲለው ስራውን ተወ፤ ለችግርም ተጋለጡ፤ በመጨረሻም ብዙም ሳይቆይ በልብ ህመም በሽታ ለህልፈት ተዳረገ፡፡

እናትም በ2008 ማለትም በ81 ዓመታቸው ከልጃቸው በፊት አለፉ፡፡ ከዚያ በኋላ እህቷ እየተንባከበቻት ለአራት ዓመታት ቆየች፡፡

ሆኖም በሽታውና ስቃዩ በርትቶባት መንቃት ባለመቻሏ እናቷ ከሞቱ ከአራት ዓመት በኋላ ከ42 ዓመታት የጽኑ ህመም ቆይታ በኋላ በ59 ዓመቷ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል፡፡

በዚህም የዓለም ጊነስ ሪከርድስ ኤድዋርዳን ራሷን ስታ (ኮማ) ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየት ሲል መዝግቤያታለሁ ብሏል ሰሞኑን፡፡

ዶ/ር ዌይን ዳየር ከማርሴለን ዳየር ጋር በመሆን “A Promise Is A Promise: Unbelievable Story of a Mother’s Unconditional Love and What It can Teach Us’’ በሚለው መጽሃፍ ውስጥ የኤድዋርዳን ታሪክ ከትቧል።

ጸሃፊው እንዳለውም ይህ ሴራ ቀመስ የሆነ ታሪክ አይደለም፤ ወይንም በፍቅር ስለከነፉ ጥንዶች የሚያትት ልብ ወለድ መጽሃፍ አይደለም፡፡ እውነተኛ ጽናትና ፍጹም ፍቅር የታየበት እናትነት ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!