አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት 3 ሺህ 125 ኩንታል ከርቤ፣ አበከድ፣ ዕጣን እና ሙጫ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረቡን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ጋሻው አይችሉህም እንዳሉት÷ 2 ሺህ 275 ኩንታል ለሀገር ውስጥ እንዲሁም 850 ኩንታል የተፈጥሮ ሙጫ ምርት ለውጭ ገበያ ቀርቧል፡፡
ለሀገር ውስጥ ገበያ ከቀረበው 15 ሚሊየን 142 ሺህ ብር እና ለውጭ ገበያ ከቀረበው ደግሞ 24 ሚሊየን 191 ሺህ ብር መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የተፈጥሮ ሙጫ ምርቶች በአብዛኛው የሚሰበሰቡት ከ1 ሺህ 500 ሚሊ ሜትር የባህር ጠለል በታች በሆኑ የትግራይ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች ቆላማ አካባቢዎች ከሚገኙ የተፈጥሮ ደኖች መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምርቶቹ ለጨርቃ ጨርቅ፣ መድኀኒት፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ቀለም፣ ኮላ፣ ከረሜላ፣ ሰንደል፣ ኮስሞቲክስ (ሽቶ) እና ለሌሎች የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት እንደሚውሉም አስረድተዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከሚሰበስበው የዕጣን ምርት ከ80 በመቶ በላይ ያህሉ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብና ዋነኛ መደራሻዎቹም÷ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ግሪክ፣ ቡልጋሪያ፣ ቱኒዝያ፣ ግብጽ እና ኔዘርላንድስ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ኮርፖሬሽኑ ከውጭ ሀገር ለሚያስመጣቸው የእርሻ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች ግዥ መደጎሚያነት ይውላል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ከ11 ሺህ 440 በላይ ኩንታል የተፈጥሮ ሙጫ ምርት በክምችት እንደሚገኝ እና ይህም ከ93 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ እንዳለው አመላክተዋል፡፡
ምርቱን ለገበያ በማቅረብ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንዳሉ ገልጸው÷ በዘርፉ የግብይት ሥርዓት ባለመኖሩ ከምርቱ የሚፈለገው ጥቅም አለመገኘቱን ጠቁመዋል።
ሕገወጥ ግብይት እና የደን ውጤቶች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር በማጋጠሙ ምርቱን በሚፈለገው መጠንና ደረጃ ለማግኘት እንዳላስቻለም ተናግረዋል።
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!