Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው ከነበሩ 400 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ከ 350 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ የኢትዮጵያ ታምርት  ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አስፋው አበበ ÷ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 85 በመቶ እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በንቅናቄው በአንድ አመት ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ገቢ ምርቶች በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን የገለፁት አስተባባሪው ÷የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ አሁን ላይ ከ 53 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪዎችን መሰረታዊ ችግሮች በመፍታት አቅማቸውንም ማሳደግ ይቻል ዘንድ የክላስተር ኮሚቴ መቋቋሙንም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

በ10 አመቱ እቅድ ደግሞ በአምራች ኢንዱስትሪው  ከ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር  እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዙፋን ካሳሁን

Exit mobile version