የሀገር ውስጥ ዜና

የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ የአገልግሎት ስርዓት ይፋ ሆነ

By Feven Bishaw

May 08, 2020

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የአገልግሎት ስርዓትን በይፋ አስጀመረ።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሳንዶካን ደበበ እንዳሉት፥ አገልግሎቱ በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከሚሰጡ በርካታ አገልግሎቶች ለጊዜው በተወሰኑ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የሚሰጥ ነው።

በዚህም ህብረተሰቡ በአካል ወደ ተቋሙ መምጣት ሳያስፈልገው አገልግሎት የሚያገኝበትና ክፍያ የሚፈጽምበት በመሆኑ ጊዜን፣ ጉልበትንና ወጪን የሚቆጥብ ሥርዓት መሆኑን አስረድተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ አሰራሩ ለዚህ ደረጃ እንዲደርስ የትራንስፖርት ዘርፉ አመራር ላሳየው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።

ቴክኖሎጂው ለአጠቃቀም ቀላል፣ በቤት ሆኖ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችልና ለሀገር ውስጥ ችግር ሀገራዊ መፍትሔ መፈለግን ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው በትራንስፖርት ዘርፉ ከ26 በላይ አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት ከታቀደው አንፃር ብዙ ስራ ይቀራል ብለዋል።

ቢሆንም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለትራንስፖርት ዘርፉ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የትራንስፖርት አገልግሎትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ይህን ጅማሮ በአጭር ጊዜ ሥርዓት በማበጀት በማስረከቡ አመስግነዋል።

በተክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መሰጠቱ በአካል መምጣትን በማስቀረት ጊዜና ወጪን የሚቆጥብ እንደሆነ መናገራቸውን ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።