አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤተሰብ አባላት በተለያዩ የህይወት ገጠመኞች መለያየት እንደሚገጥም እሙን ነው፡፡
በፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት መለያየት ወይንም መራራቅ ሊመጣ ይችላል፡፡
ያንጊዜም ናፍቆት እና መብሰልሰሉን የህይወታቸው አንድ አካል በማድረግ በ‘’አንድ ቀን አገኘዋለሁ፤ አገኛታለሁ’’ ተስፋ ዓመታትን ይገፋሉ፡፡
ናሽናል ወርልድ አንድ ተመሳሳይ ታሪክ ባጋራበት የማህበረዊ ትስስር ገጹ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ የተለያዩ ወንድም እና እህት መገናኘታቸውን አስነብቧል፡፡
በፈረንጆቹ 1947 ደም አፋሳሽ ነበር እያሉ ብዙዎች በሚገልጹት ፓኪስታን ከሕንድ የተገነጠለችበት ጊዜ የቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤታማቾችና ጓደኛሞች ሊለያዩ ግድ ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር የአሁኑ የ80 ዓመት አዛውንት የወቅቱ የአራት ዓመት ህጻን ሲንግ ከእናቱ ጋር የተለያየው፡፡
ሲንግ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ በሕንድ ሰሜናዊ ፑንጃብ ግዛት ውስጥ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ሲኖሩ በፓኪስታን የምትኖር ታናሽ እህት እንዳላቸው በጭራሽ አያውቁም ነበር፡፡
ሳኪና ባይ የተባሉት የ68 ዓመት አዛውንት እህታቸው ታዲያ ወንድም እንዳላቸው ያውቁ ነበርና ወንድማቸውን ፍለጋ በሀገሪቱ በሚታተም ጋዜጣ በፈረንጆቹ 2016 አንድ ብለው ይጀምራሉ።
ይህን ታሪክ የሰማ ዩ ቲዩበርም የዛሬ አመት በሚጠቀምበት ዩ ቲዩብ ዜና ሰርቶ በማሰራጨት ፍለጋቸውን ያግዛቸዋል።
ይህን ዜና የተመለከተ የአካባቢው አስተዳደርም አዛውንቱን ሲንግን አፈላልጎ በማግኘት ከእህታቸው ጋር በስልክ አገናኝቷቸዋል።
አዛውንቱ ሲንግ እኔና እህቴ በእድሜ ማምሻችንም ቢሆን በመገናኘታችን ደስታዬ ወደር የለውም ሲሉ እንባ በተቀላቀለ ደስታ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡
አዛውንቱ ስሜታቸውን ሲገልጹ ህዝቦች ምንም ቢሆን ሊለያዩ አይችሉም ብለዋል፡፡
በልጀነታቸው አብረው ቦርቀው ባያድጉም የሚጣፍጥ የልጅነት ትውስታቸውን ለማጣጣም ባይታደሉም በማምሻ እድሜያቸው ተገናኝዋል።