Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አየር መንገዱ በአፍሪካ ሀገራት የመገበያያ ገንዘብ በትኬት ሽያጭ ያስገባውን ገቢ በውጭ ምንዛሬ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት የመገበያያ ገንዘብ በትኬት ሽያጭ ያስገባውን በዶላር፣ በፓውንድና በዩሮ ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አቶ መስፍን÷አየር መንገዶች በገቡት ውል መሰረት የቲኬት ሽያጭ በሀገራት የመገበያያ ገንዘብ እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ተክትሎ በሀገራት የመገበያያ ገንዘብ በሚካሄድ የቲኬት ሽያጭ የተገኘውን ገቢ ለቲኬቱ ባለቤት አየር መንገድ በዶላር፣ በፓውንድ ወይም በዩሮ ተቀይሮ ገቢ እንደሚደረግለት አንስተዋል።

አየር መንገዱ በተለያዩ ሀገራት የመገበያያ ገንዘብ ያስገባውን ገቢ በወቅቱ እየሰበሰበ መሆኑን ገልጸው÷ በአፍሪካ ሀገራት ግን አየር መንገዱ ያስገባውን ገቢ በዶላርና በዩሮ ቀይሮ በማስረከብ ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

በዚህም አየር መንገዱ በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ከትኬት ሽያጭ ያገኘው ከ180 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ እስካሁን ሳይከፈለው መቆየቱን ገልጸዋል።

ይህንንም ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቀመጫውን ካናዳ ካደረገው ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አይአታ) ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አይአታ) ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስገባውን ገቢ በዶላርና በዩሮ በሚቀበልበት ምቹ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱንም ነው ያነሱት።

ጎን ለጎንም አየር መንገዱም ከተለያዩ የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ከአገራት የኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚተሳሰር መሆኑን ጠቅሰው÷ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህን ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ሀገራት በተለይም ምጣኔ ኃብታዊ እድገታቸውን አጠናክሮ ማስቀጠልና የውጭ ምንዛሬ ግኝታቸውን በዛው ልክ ማጎልበት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

Exit mobile version