Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከውጭ የተገዛ 16 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት በቀጣዩ ሳምንት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ የተገዛ 16 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት በቀጣዩ ሳምንት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (ኢግልድ) አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በተለይም የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን ዋጋ ለማረጋጋት ኢግልድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በዚህ መሰረትም በገበያ ላይ ጥረት የሚስተዋልባቸውን ምርቶች ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይም በ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ 16 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ግዢ ከውጭ ሀገር መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

የተገዛው የምግብ ዘይትም በቀጣዩ ሳምንት ወገ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡

ዘይቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚከፋፈልም አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version