የሀገር ውስጥ ዜና

የህይወት አድን ምግቦች ያልተገባ አጠቃቀም በጤና አገልግሎት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ነው ተባለ

By Amele Demsew

August 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 ኤፍ ቢ ሲ) የህይወት አድን ምግቦች ያልተገባ አጠቃቀም በምግብ አለመመጣጠን የጤና አገልግሎት አሰጠጥ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

የጤና ሚኒስቴር የምግብ አለመመጣጠን የጤና አገልግሎትን ወደ መደበኛ የጤና ፕሮግራም ማስገባት የሚያስችለውን ስምምነት ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ከዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም እና ከተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

የመግባቢያ ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከተቋማቱ ኃላፊዎች ጋር ተፈራርመዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ለህክምናው የሚሆኑ ግብአቶች በህገ-ወጥ መንገድ በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው÷ ይህም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አንስተዋል።

ህገ-ወጥ ድርጊቱ ከወንጀልነቱ በተጨማሪ ጤናማ ሰው ቢጠቀማቸው ለሌላ የጤና መዛባት የሚዳርጉ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

እነዚህ በለጋሽ አካላት የሚመጡ ግብአቶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ መዋል እንዳለባቸው ገልጸው ÷ በህገ-ወጥ ድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ጄኒፈር ቢቶንዴ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል የሰራችውን ስራ አድንቀዋል።

ስምምነቱም ለቀጣይ ተግባራት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው ÷ለጤና አገልግሎቱ የሚደረጉ ድጋፎች ለሚመለከታቸው ሰዎች መድረሱን የማረጋገጥ ስራም የጋራ ጥረትን እንደሚጠይቅ አንስተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት የፕሮግራሞች ምክትል ተወካይ ማሪኮ ካጎሺማ ስምምነቱ በምግብ እጦት ማንም እንዳይጎዳ በጋራ መነሳታችን ማሳያነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡