Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መንግስት በትግራይ ክልል የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በትግራይ ክልል የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ጠየቀ።

የቢሮው የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሚኪኤለ ሙሩፅ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በክልሉ ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ የአፍሪካ ተምች ተከስቶ እንደነበር ጠቁመዋል።

በክልሉ በ31 ወረዳዎች በሚገኙ 126 የገጠር ቀበሌዎች በ28 ሺህ 41 ሄክታር የእርሻ መሬት እና 1 ሺህ 611 ሄክታር የግጦሽ መሬት ላይ ተከስቶ የነበረውን ተምች በባህላዊ መንገድ እና ኬሚካል በመርጨት መቆጣጠር መቻሉን አውስተዋል።

በተመሳሳይ ‘በርኖስ’ የሚባል የተምች አይነት በክልሉ 5 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 9 ወረዳዎች ተከስቶ እንደነበር የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፥ በባህላዊ መንገድና ኬሚካል በመርጨት መከላከል መቻሉንም ነው የገለጹት።

በተያያዘም በክልሉ ሰሜን ምዕራብ ዞን ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ የአንበጣ መንጋ በአምስት ወረዳዎች ተከስቶ፥ በፍራፍሬ እና በእንስሳት መኖ ላይ ከፍተኛ ውድመት ማስከተሉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ምስራቅ፣ ደቡብ ምስራቅ እና ደቡብ ዞኖች የበረሃ አንበጣ መንጋ መከሰቱንም ነው የተናገሩት።

የአንበጣ መንጋው ከሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱን ገልጸው፥ በተለይም ወደ ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች የሚመጣው የአንበጣ መንጋ በአፋር ክልል ከሚገኙ ያለው፣ መጋለ እና ኮኮባ የሚባሉ አካባቢዎች የተፈለፈለ መሆኑን አስረድተዋል።

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልም በባህላዊ መንገድ እና ኬሚካል በመርጨት የመከላከል ስራ እየተሰራ ቢሆንም፥ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አዳጋች መሆኑንም ነው የገለጹት።

የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር በፌደራል መንግስቱ የተዋቀረ ቡድን በክልሉ ተገኝቶ የልየታና የጥናት ስራ እየሰራ ሲሆን፥ የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም በጉሎመኸዳ እና ኢሮብ አካባቢዎች የፌደራሉ መንግስት አንበጣውን በመከላከልና በመቆጣጠር እገዛ እንዲያደርግም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

Exit mobile version