የሀገር ውስጥ ዜና

የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚያስችል የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ሊደረግ ነው

By Amele Demsew

August 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚያስችል የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በተመለከተ የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ በሰጡት መግለጫ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያየለ የመጣውን የዋጋ ንረት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቆጣጠር የብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል።

የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንና ውሳኔዎቹም ቅንጅታዊ ስራውን እንደሚያግዙ ገልጸው፤ ከውሳኔዎቹ መካከል ለመንግስት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር ባለፈው አመት ከተሰጠው ከ1/3ኛ እንዳይበልጥ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

መንግስት ቅድሚያ የግምጃ ቤት ሰነድ አማራጭን አሟጦ እንዲጠቀምና አማራጭ ሳይኖር ሲቀር ብቻ የቀጥታ ብድር እንደሚጠቀም ተጠቁሟል።

በ2016 ዓ/ም በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የሃገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንደሚገደብ ተነግሯል።

በመሆኑም ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሰረት እንዲያስተካክሉ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከብሄራዊ ባንክ ከሚወስዱት ብድር የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል እንደሚደረግም ተነስቷል፡፡

ቁልፍ የሆኑ የወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዘርፎች በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ላኪዎችን ለማበረታታት ከዚህ ቀደም የነበረው የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል ይደረጋል ተብሏል።

ላኪዎቹ 50 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ እንዲያስገቡ፣ 10 በመቶውን አብረው ለሚሰሩት ባንክ እንዲሰጡ እና 40 በመቶውን ለራሳቸው እንዲጠቀሙ ተወስኗል።

የዋጋ ንረቱን በመቆጣጠር ረገድም፤ በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የዋጋ ንረቱ ከ20 በመቶ በታች እንዲሆንና በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ይሰራል ብለዋል የብሄራዊ ባንክ ገዥው ማሞ ምህረቱ።

ህብረተሰቡ ውሳኔውን በመደገፍ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን እርምጃ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

በበርናባስ ተስፋዬ