የሀገር ውስጥ ዜና

ከህግ አግባብ ውጪ ሲሰሩ በተገኙ 107 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

By Mikias Ayele

August 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከህግ አግባብ ውጪ ሲሰሩ በተገኙ 107 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸው ንግድ ድርጅቶች ከተሰጣቸው የንግድ ፈቃድ መስኮችና ዓላማዎች ውጪ ሲሰሩ የነበሩ፣ ለኢንስፔክሽን ስራ ፍቃደኛ ያልሆኑ እና ባልፀና ወይም ባልታደሰ ንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ባስመዘገቡት የስራ አድራሻ ያልተገኙ እንዲሁም የቅርንጫፍ አድራሻ ያላስመዘገቡ ድርጅቶች እንደሚገኙበት ተመላክቷል።

ሚኒስቴሩ ባደረገው ክትትልም በ49 ንግድ ድርጅቶች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን በ58 ንግድ ድርጅቶች ላይ ደግሞ የእግድ እርምጃ ተወስዷል፡፡

በቀጣይም በንግድ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው የቁጥጥርና የክትትል  ስራ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡