የሀገር ውስጥ ዜና

125 አዳዲስ የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆኑ

By Amele Demsew

August 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 125 አዳዲስ የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ የተቋሙን የ2015 የስራ አፈፃጻም እና የ2016 እቅድ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም÷ አገልግሎቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 35 ቢሊየን 458 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ገቢውን ወደ 45 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለማሳደግ መታቀዱንም አመላክተዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሪፎርም ስራወች እየተከናወኑ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

13 ሪጅኖች፣ 26 ዲስትሪክቶች፣ 582 አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እና 6 ሺህ 448 ሳተላይት መለያዎችን በማዋቀር ለደምበኞች አገልግሎት መሰጠቱንም ነው የጠቀሱት፡፡

600 ሺህ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደምበኞችን ተደራሽ ለማድረግ ስለመታቀዱም ነው የገለጹት፡፡