አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታማኝነት ግዴታቸውን ለተወጡ ግብር ከፋዮችና ባለድርሻ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
“ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ቃል ለ2ኛ ጊዜ በተካሔደው የዕውቅናና የምስጋና መርሐ-ግብር ላይ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ-ግብሩም በታማኝነት ግብርን በመክፈል ግዴታቸውን ለተወጡ ግብር ከፋዮችና ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷል፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ግብር ተሰብስቧል፡፡
የክልሉን ግብር የመሰብሰብ አቅም አሁን ካለው የልማት ፍላጎት ጋር እኩል በማዛመድ ሕገ-ወጥነትን ከመቆጣጠር ባሻገር ቅንጅታዊ አሠራርን ማጎልበት እንደሚገባ ማንሳታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ ዕውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች በበኩላቸው÷ ግብርን በታማኝነት መክፈል ሀገራዊ ግዴታን መወጣት መሆኑን ጠቁመው፣ የዕውቀና መርሐ-ግብሩን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡