የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሌጆች የቀድሞ ታጣቂዎች በመልሶ ግንባታ ስራ እንዲሰማሩ የማድረግ የጎላ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል- ጀ/ል ታደሰ ወረደ

By Amele Demsew

August 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ታጣቂዎች ሙያዊ ክህሎት ተላብሰው በመልሶ ግንባታ ስራ እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ኮሌጆች ድርሻ የጎላ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ም/ርዕሰ መስተዳድር ጀነራል ታደሰ ወረደ ገለጹ።

በክልሉ የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ዘርፉን ስራ ለማስጀመር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ም/ ርዕሰ መስተዳድር ጀነራል ታደሰ ወረደ እንዳሉት÷ በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ የመንግስትና የግል ሙያና ቴክኒክ ስልጠና ኮሌጆች ፈጥነው ወደ ስራ ሊገቡ ይገባል።

ኮሌጆቹ ወጣቶች ሙያዊ ክህሎት በመላበስ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የማድረግ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

በተለይም ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለከሱ የቀድሞ ታጣቂዎች ሙያዊ ክህሎት ተላብሰው በሙሉ አቅማቸው በመልሶ ግንባታ ስራ እንዲሳተፉ የማድረግ የጎላ ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

“የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ ሲገቡ በሙያና ቴክኒክ ሰልጥነው ወደ ሰራ እንደሚሰማሩ መንግስት ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል” ብለዋል ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ቢሮ የስራ እድልና ፈጠራ ዳይሬክተር ገነት አረፈ በበኩላቸው ÷ኮሌጆቹ የሚሰጧቸው የሙያ ስልጠናዎች ለውጥ ማምጣት የሚችሉ እንዲሆኑ ባለሀብቶች፣ ዳያስፖራዎችና ባለድርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

የመንግስትና የግል ኮሌጆቹ በመደበኛና በአጭር ስልጠናዎች በየአመቱ ለ111ሺህ ወጣቶች ሙያዊ ስልጠና የመስጠት አቅም ያላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!