Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በ2015 በጀት ዓመት በአምራች ኢንተርፕራይዞች 122 ሺህ በላይ የሥራ እድል ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለ122 ሺህ 380 ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ መጅዲያ ሐቢብ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ በ2015 በጀት ዓመት ኢንተርፕራይዞች በተኪ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ በትኩረት ተሰርቷል፡፡

በዚህም በተለያዩ ዘርፎች በተኪ ምርቶች ላይ የሚሰማሩ አነስተኛ ፣መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ነው ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተሰራ የቅንጅት ስራ 799 አነስተኛ ኢንተፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢተርፕራይዝ መሸጋገራቸውን አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይ 77 መካከለኛ ኢተርፕራይዞች ወደ ከፍተኛ መሸጋገራቸውን ጠቁመው÷ በዚህ ረገድም የአቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም እና ነባሮችን በማጠናከርም ለ122 ሺህ 380 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የኢንተርፕራይዞችን የማምረት አቅም ለማሳደግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡

መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የማምረቻ፣ ማሳያና መሸጫ ማዕከላትን የማዘጋጀትና የማልማት ስራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version