የሀገር ውስጥ ዜና

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ36 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸው ተገለጸ

By Amele Demsew

August 04, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተያዘው የክረምት ወቅት ከ36 ሚሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፥ የክረምት ችግኝ ተከላ በይፋ ከተጀመረበት አንስቶ እስከ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ ከ36 ሚሊየን በላይ ችግኞች መትከል ተችሏል፡፡

በክልሉ ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 2016 ዓ.ም ባሉት የክረምት ወራት 55 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ብቻ በክልሉ 10 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከ14 ሚሊየን በላይ ለመትከል መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡

ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ ከ32 ሚሊየን በላይ በጥምር ደን ልማት የተተከሉ የዛፍ ዝርያዎች እንደሆኑ የጠቆሙት ሃላፊው ቀሪዎቹ ቡና፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ዘይቱን እና ሌሎች የፍራፍሬ ዝርያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በችግኝ ተከላው ከ700 ሺህ በላይ የክልሉ ህዝብ ተሳታፊ መሆኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡