Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የአልባሳት ግዢ ጋር ተያይዞ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ ነው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ የታዘዘው።

ተከሳሾቹ 1ኛ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ፣ 2ኛ የተቋሙ የመንግስት የግዢ ዳይሬክተር ግሩም ወልዴ፣ 3ኛ የኮሚሽኑ የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ደረጄ ተፈራ፣ 4ኛ የኮሚሽኑ የሎጀስቲክስ ምዝገባና ቁጥጥር ባለሙያ ወንድሜነህ ምስጋናው፣5ኛ የአደጋ ስጋት ትግበራ ቡድን መሪ እዮብ ታደሰ ካሳ ፣6ኛ በኮሚሽኑ የህክምና ባለሙያዋ ሲስተር አልማዝ ጌቶ፣ 7ኛ የአደጋ መረጃ ሀርድ ዌርና ሶፍትዌር ባለሙያ መስፍን ለገሰ እና 8ኛ ነጋዴ የሆኑት ንጉስ አማን የተባሉ ተከሳሾች ናቸው ።

ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል 1ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን÷ ቀሪ ተከሳሾች ቀርበዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ባቀረበው የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ላይ እንደተመላከተው በሰኔ ወር በ2014 በጀት አመት ተከሳሾቹ የግዢ ጨረታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍና በስውር በመመሳጠር ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸው ነው የተገለጸው፡፡

በወቅቱ በተደረገ የገበያ ዳሰሳ ጥናት የአልባሳቱ ዋጋ 46 ሺህ 923 መሆኑ እየታወቀ ተከሳሹቹ ግን ብልዶዘር የተሰኘ የእሳት አደጋ መከላከያ ልብስን ከፍተኛ በሆነ ዋጋ ማለትም በፍሬ 184 ሺህ 644 ብር ከ8ኛ ተከሳሽ ተጫራች ድርጅት ግዢ እንዲፈጸም በማፅደቅ አጠቃላይ 217 ፍሬ አልባሳትን በ40 ሚሊየን 67ሺህ 748 ብር መግዛታቸው ተጠቅሷል፡፡

በዚህም በመንግስት ላይ በልዩነት 29 ሚሊየን 885ሺህ 441 ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ተብሎ በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሶ ነበር ።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በችሎት ከተነበበላቸው በኋላ የዋስትና መብት ይከበርልን ጥያቄ አቅርበዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ÷ የቀረበባቸው የከባድ ሙስና ክስ አንቀጹ ዋስትና እንደማያሰጥ ገልጾ ተከራክሯል።

ክርክሩን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው የቾሎት ቀጠሮ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ወደማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል።

ተከሳሾቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤህግ ምስክሮች እንዲሰሙለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ቃል ለመስማት ለጥቅምት 7 እና 8 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version