አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በቀረበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015 ላይ ነው፡፡
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማስክበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ፥ ይህ እንቅስቃሴ የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወከ እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ፤ የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም ህግ እና ስርዓት ለማስከበር የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፣ እንቅስቃሴው በሃገር ደህንነት እና በህዝብ ሰላም ላይ የደቀነው አደጋ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መጥቷል፡፡
መንግስት ትጥቅ አንስተው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ሁሉ የሰላም እና ህጋዊ መንገድን እንዲከተሉ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
የታጠቁ ፅንፈኛ ቡድኖች እየፈፀሙ ባለው ጥቃት ምክንያት የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡
የክልሉ መንግስትም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለ የሚገኝ መሆኑን በመግለጽ፥ ሁኔታውን በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ፣ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት እንዲደነግግ እና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ አቅርቧል።
በመደበኛ የህግ ስርዓትን መሰረት አድርጎ ይህን ፈር የለቀቀ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አዳጋች ሁኔታ በመፈጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ህገመንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ላይ የተቃጣ አደጋን በመደበኛ የህግ ስርዓት ለመቆጣጠር ባልተቻለ ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ህገመንግስታዊ ስርዓትን ከአደጋ የመከላከል ስልጣን እንዳለው በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 93 (1) ተደንግጓል፡፡
በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በህገመንግስቱ የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ስላለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 እንዲታወጅ በሙሉ ድምጽ ወስኗል ፡፡
ምክር ቤቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ የተወያየ ሲሆን፥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን የሚያካሂዱ እንዲሆኑ ለማስቻል የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አዋጅ መውጣቱ ይታወቃል፡፡
በዚሁ መሰረትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ሆኖ አካዳሚያዊ እና አስተዳደራዊ ነፃነቱ ተጠብቆ መንቀሳቀስ እንዲችል፥ በትምህርት ዘርፍ ለተጀመረው የሪፎርም እንቅስቃሴ ፈር ቀዳጅ ሆኖ፣ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ስርዓትን ተግባራዊ እንዲያደርግ እና ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተምሳሌት እንዲሆን አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡