Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በ2015 በጀት ዓመት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ፡፡

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ የክልሉን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በተለይም ሰላምን ከማስፈን እና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ 1 ቢሊየን 361 ሚሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ቢሊየን 530 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ጠቁመዋል።

በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በተከናወኑ ሥራዎችም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ነው የጠቆሙት።

በሌማት ትሩፋት፣ መስኖን በማጎልበት እና በገበያ ተኮር ሰብሎች ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ሥራዎችም አበረታች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በዓመቱ በአጠቃላይ ለ9 ሺህ 696 ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ8 ሺህ 459 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

ከ130 ሺህ በላይ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሐረር ከተማን እንደጎበኙና ከዚህም ከ112 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version