Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠል አለበት – ዶክተር ሊያ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ህብረተሰቡ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ከግምት በማስገባት የሚያደርገውን ጥንቃቄ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ።

ዶክተር ሊያ ለአዜአ እንደተናገሩት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 1 ሺህ 382 ሰዎች መካከል 17 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ይህም በኢትዮጵያ እስካሁን በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡን ጠቅሰው፥ ”በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች ቁጥር 162 አድርሶታል” ብለዋል።

እስካሁን የተመዘገቡትና የተገለጹት ቁጥሮች ትክክለኛ አሃዝ አያሳዩም ያሉት ሚኒስትሯ፥ “የምናውቀው የመረመርነውን ብቻ ነው፤ የመረመርነው ደግሞ ትንሽ ነው” ብለዋል።

ስለዚህ ወረርሽኙን መርሳትና መዘናጋት እንደማይገባና ኅብረተሰቡም ቁጥሩ “ያነሰው በሽታው እኛ ጋር ስላልመጣ ወይም ስለማይመጣ” እንዳልሆነ ሊገነዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኬንያና ሱዳን በመጀመሪያዎቹ ቀናት ትንሽ ቁጥር ማስመዝገባቸውን ተከትሎ መዘናጋት መታየቱን አስታውሰው ሁኔታው ”ዋጋ አስከፍሏቸዋል” ነው ያሉት።

ሕዝቡም ከጎረቤት ሃገራት፥ መዘናጋት ትልቅ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል በመማር የሚደረጉትን ጥንቃቄዎች ማጠናከር እንደሚገባው አውስተዋል።

“ትክክለኛ ትምህርትና እርምጃ ለመውሰድ፣ በብዙ ቁጥር መያዝ፣ በብዙ ቁጥር መሞት የለብንም” ያሉት ሚኒስትሯ፥ ያለው ብቸኛ አማራጭ መጠንቀቅ በመሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

Exit mobile version