አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በነሐሴ ወር በኢትዮጵያ ተፋሰሶች ላይ የሚኖረውን ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት ተከትሎ ሊፈጠር ከሚችል ቅጽበታዊ ጎርፍ መጠንቀቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመጪው ነሐሴ ወር በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ስፍራዎች ካለፈው ወር አኳያ በዝናብ ስርጭቱ ላይ በአንጻራዊነት የመዳከም አዝማሚያ ሊኖር እንደሚችል ጠቁሟል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በተጠቀሱት ስፍራዎች የሚገኘው የእርጥበት መጠን የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚኖረውና ይህም ለአካባቢው የግብርና እንቅስቃሴ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አመላክቷል።
ያም ሆኖ በአካባቢው የሚገኘውን አነስተኛ እርጥበት አርሶ አደሩ በተገቢው መንገድ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ይገባል ነው ያለው።
በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው፣ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች የተነሳ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ሊኖር እንደሚችልም ተገልጿል።
ይህም ለእጽዋት ልምላሜና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው ኢንስቲትዩቱ ያመለከተው።
በሌላ በኩል በነሐሴ ወር የክረምት እርጥበት ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ የዝናብ ስርጭት ከፍተኛ እንደሚሆን ነው የትንበያ መረጃው የሚያሳየው።
በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በመካከለኛው እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ተፋሰሶች የዝናብ ሁኔታው እየተጠናከረ እንደሚሄድም ተመላክቷል።
በአብዛኛው አባይ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ አፋር ደናክል፣ የላይኛውና የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው ዋቢ ሸበሌና ገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ላይ የተሻለ እርጥበት እንደሚኖርም ተጠቁሟል።
ሊኖር ከሚችለው ከፍተኛ ዝናብ ጋር ተያይዞ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶችና ንዑስ ተፋሰሶች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የወንዞች ሙላት ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ራሱን ሊደርስ ከሚችል ድንገተኛ ጉዳት እንዲጠብቅም አሳስቧል።