Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በበጀት ዓመቱ ከኢንዱስትሪ ምርቶች የወጪ ንግድ 450 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም ከኢንዱስትሪ ምርቶች የወጪ ንግድ 450 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በ2015 እቅድ አፈፃፀምና በ2016 ዓ.ም እቅድ ውይይት ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት ÷450 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬን ከማግኘት ባሻገር 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ተኪ ምርት በሀገር ውስጥ ለማምረት ታቅዷል፡፡

ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ነው ሚኒስትሩ የገለፁት፡፡

አቶ መላኩ የኢንዱስትሪ ዘርፍን ውጤታማ ለማድረግ ባንኮች ለአምራቾች የሚያዘጋጁትን ብድር ከፍ እንዲያደርጉ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ በተሻለ መልኩ ለአምራቾች ብድር እያቀረቡ የሚገኙት የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

አምራቾች ብድር ሲጠይቁም አስፈላጊውን መስፈርት ሟሟላት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የዘርፉ አስፈፃሚ አካላት ለአምራቾች ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ የሰው ሀይል አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጽያ ታምርት ንቅናቄ የተገኘውን ውጤት ማስቀጠል ብሎም የግሉ ዘርፍ ንቅናቄውን እንዲያስቀጥል መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በርካታ አምራቾች ወደ ምርት እንዲገቡ ቢደረጉም ስትራቴጂክ ጠቀሜታ እያላቸው ወደ ስራ ያልገቡ እንዳሉ በማንሳት እነዚህን አምራቾች ወደ ስራ ሊመለሱ ይገባል ብለዋል፡፡

በኤፍሬም ምትኩ

Exit mobile version