Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የወባ እና ኮሌራ በሽታዎች ስርጭት መጠን መጨመሩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባ እና ኮሌራ በሽታዎች የስርጭት መጠን መጨመሩን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ የወባ እና የኮሌራ በሽታ ስርጭት መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

ስርጭቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአለምአቀፍ ደረጃም የጨመረ መሆኑን ያነሱ ሲሆን÷ ከባለፈው አመት በ15 ሚሊየን ከፍ ማለቱን አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በድርቁ ወቅት የተፈጠሩ ችግሮች እና ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የዝናብ ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎች መኖር የወባ እና የኮሌራ በሽታዎች እንዲቀሰቀሱ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ሌላኛው ለስርጭቱ መጨመር ምክንያት የሆነው የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን ላይ ፈጥኖ በመድረስ መቆጣጠር አለመቻሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሌራ በአምስት ክልሎች መከሰቱን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው÷ በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ሲዳማ ክልሎች ወረርሽኙን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ቀሪ ክልሎች ላይም የቁጥጥር ስራው ተግባራዊ እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቁመው እስካሁን ከ2ሚሊየን በላይ ክትባት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃይ ዜጎች ባሉባቸው ቦታዎች ስርጭቱ እዳይባባስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ነው በቆይታቸው የተናገሩት፡፡

የወባ መድሀኒት አቅርቦት ቸግር የለም ያሉት ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ከስርጭት ጋር ተያይዞ ግን አንዳንድ ቦታዎች እጥረቶች መከሰታቸውን አንስተዋል፡፡

ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በማርታ ጌታቸው

Exit mobile version