የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ሩሲያ የባዮሎጂካል ሳይንስ የጥናትና ምርምር ማዕከል በጋራ ለማቋቋም ተስማሙ

By Amele Demsew

July 27, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በባዮሎጂካል ሳይንስ የጥናትና ምርምር ማዕከል በጋራ ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከሩሲያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ቫለሪ ፋልኮቭ ጋር ተፈራርመዋል።

የሩሲያ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ከ 35 ዓመታት በላይ በስነ ህይወት ዙሪያ ጥናትና ምርምር ሲያደርጉ መቆየታቸው ተመላክቷል።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ÷የአሁኑ ስምምነት ከዚህ በፊት ሩሲያውያን ተመራማሪዎች ሲያካሂዱ የቆዩትን ጥናት አድማስ ለማስፋት ያለመ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዞህ ባለፈም ምርምሮቹ ተቋማዊ ባለቤትነት ኖሯቸው ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀገራቱ ማዕከሉን በጋራ አቋቁመው ወደ ተግባር ሲገቡ በዘርፉ ያለው የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያስፋፋ ተጠቁሟል፡፡