Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በየደረጃው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል መረባረብ ይገባል-አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 27፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር መንግስት በሚያደረገው ጥረት መልካም ጅምሮች ቢኖሩም፤ በተግባር ሂደት እየፈተኑ የሚገኙ ችግሮችን በጋራ በመረባረብ በፍጥነት መሻገር እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳስበዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት÷የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም አስመልክቶ ከክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በቪዲዩ ውይይት  ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

ህብረተሰቡ ለጥንቃቄ የሚሰጡ መመሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሚስተዋሉ  ውስንነቶች እና ችግሩን አቅልሎ የማየት አዝማሚያ ፈጣን የባህሪ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መስራት እንደሚጠይቅ በዚሁ ወቅት አንስተዋል።

አቶ ደመቀ አያይዘውም  በተግባር ሂደት በየደረጃው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በቀጣይ ወረርሽኙ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል እና የከፋ ዋጋ እንዳያስከፍል በጋራ እንደሚረባረቡ  አሳስበዋል።

የክልል ከፍተኛ አመራሮች በበኩላቸው ÷ወረርሽኙን ለመግታት የሚያግዙ አደረጃጀት ፈጥረው አዋጁን ተከትሎ የወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑ መግለጻቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የፌስ ቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version