Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ ተጨማሪ አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ህይወቱ አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ተጨማሪ አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ ህይወቱ ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

ባለፉት 24 ሰዓታት ለ1 ሺህ 47 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 5 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውም ዶክተር ሊያ አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳስታወቁት፥ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው አምስቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የ25 ዓመት እና የ22 ዓመት ኢትዮጵያውያን በአፋር ክልል የሚገኙ ሲሆን፥ ከጅቡቲ የተመለሱ እና በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ሁለቱ ደግሞ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ባቱ ከተማ የሆኑ የ8 ዓመት እና የ19 ዓመት ሴቶች ሲሆኑ፥ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

የ75 ዓመት ኢትዮጵያዊት ሴትም ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል። የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሲሆን፥ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በመጣራት ላይ መሆኑን በመግለፅ በጤና ተቋም ተኝተው ከሚታከሙ ህሙማን ከተወሰደ ናሙና የተገኘ መሆኑንም አስታውቅዋል።

ታማሚዋ በተጓዳኝ ህመም ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ባጋጠማቸው የመተንፈስ ችግር በኮሮናቫይረስ ተጠርጥረው ናሙና ተወስዶ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከመረጋገጡ በፊት ህይወታቸው ማለፉንም ገልፀዋል።

ይህንን ተከትሎም በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 4 መድረሱንም ዶክተር ሊያ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።

ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ተጨማሪ 16 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸውንም ዶክተር ሊያ የገለፁ ሲሆን፥ ይህንን ተከትሎም በአጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 91 መድረሱን አመላክተዋል።

አሁን ላይ በአጠቃላይ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 145 የደረሰ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 48 ሰዎች በለይቶ ህክምና ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

Exit mobile version