አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅግጅጋ ከተማ የገበያ ማዕከል ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ንብረት መውደሙን የድጋፍ አሰባሳቢና የተቃጠለው ንብረት አጣሪ ኮሚቴ አስታውቋል።
በከተማዋ በተለምዶ ታይዋን ተብሎ በሚታወቀው የገበያ ማዕከል ላይ ሰኔ 30 ቀን 2015 ምሽት 5 ሰዓት ገደማ በተከሰተው የእሳት አደጋ በንግድ ሱቆችና ንብረት ላይ ውድመት መድረሱ ይታወሳል፡፡
በዚህም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሼህ አብዱልቃድር ሁሴን በተደረገው ማጣራትና ቆጠራ መታወቁን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ኮሚቴው ከባለሃብቶች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ከተለያዩ ባንኮች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መገባቱን ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ድረስም 102 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተቃጠለው የገበያ ማዕከል ላይ ሃብት ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች እንዲረዱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ባንኮች በተከፈቱ የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።