አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ አማራ ክልል ከመጡ ጎብኚዎች ከ4 ቢሊየን 796 ሚሊየን 625 ሺህ ብር በላይ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ እምቢአለ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 13 ሚሊየን 505 ሺህ 717 ጎብኚዎች በክልሉ ጉብኝት አድርገዋል።
ክልሉን የሚጎበኙ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር 9 ሚሊየን 122 ሺህ ለማድረስ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው÷ ጎብኚዎችን 13 ሚሊየን 484 ሺህ 435 በማድረስ ከዕቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡
ክልሉን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች 103 ሺህ 138 ለማድረስ መታቀዱን የገለጹት አቶ አበበ÷ 21 ሺህ 282 የውጭ ጎብኚዎች ክልሉን እንደጎበኙና አፈጻጸሙ 21 በመቶ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮሮና ወረርሽ እና በነበረው ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የተከናወኑ ሥራዎች ስኬታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር በተያያዘም÷ ለ9 ሺህ 147 ቋሚ እና ለ23 ሺህ 606 ወገኖች ጊዜያዊ ሥራ ዕድል መፈጠሩን አመላክተዋል፡፡
ቢሮው ለጎብኚ አገልግሎት ሰጭ ማኅበራት እና ለቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የሙያ ድጋፍና ክትትል ሥራውን በንቃት ስለማከናወኑም ነው የተናገሩት፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!