ዓለምአቀፋዊ ዜና

በግሪክ የሰነበተው የሙቀት ማዕበል ያስከተለው ሰደድ እሳት እየተባባሰ መሆኑ ተነገረ

By Alemayehu Geremew

July 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግሪክ የሰነበተው የሙቀት ማዕበል ያስከተለው ሰደድ እሳት እየተባባሰ መሆኑ ተነገረ።

ለቀናት ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ የሰነበተውን ሰደድ እሳት ማጥፋት ባለመቻሉ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች መሸሽን መርጠዋል ነው የተባለው፡፡

አሁን ላይ እንደተሰማው ኮርፉ እና ኢቪያ በተባሉ ደሴቶች ላይ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

በተመሳሳይ በሮድስ ደሴት የተነሳው ሰደድ እሳትም እየተባባሰ እና ጥብቅ ደኖችን ጭምር እያቃጠለ መጓዙን ቀጥሏል ነው የተባለው፡፡

የሚያደርጉት የጠፋቸው የደሴቷ ነዋሪዎች ፎጣዎቻቸውን ውሃ እየነከሩ አንገቶቻቸው ላይ በማድረግ ወደ መኖሪያቸው እየተቃረበ የመጣውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት ታግለዋል ነው የተባለው፡፡

የእሳት ማጥፊያ አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮችም ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት ሞክረዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረትም ከ10 አባል ሀገራት 500 የእሳት አደጋ ተከላካዮችን፣ 100 ተሽከርካሪዎችን እና ሰባት አውሮፕላኖችን አስተባብሮ ልኳል፡፡

ቱርክ፣ እስራዔል እና ግብፅ እርዳታ ከላኩ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ የተመዘገበው የሙቀት ማዕበል ተመልሶ ከ40 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ መድረሱንም ፒ ኤስ ቢ የተባለው የዜና ምንጭ ዘግቧል፡፡