አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ዓለምን እየፈተነ የመጣውን የማዕድናት ግብዓት እጥረት ለመቅረፍ ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ ባትሪዎችን በመሰብሰብ አድሳ ዳግም ለአገልግሎት እያበቃች እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ቻይና በዘርፉ ከ10 ሺህ በላይ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ጣቢያዎችን ከፍታ የተጣሉ ባትሪዎችን በማደስ መልሳ ጥቅም ላይ እያዋለች መሆኑን የሀገሪቷ የኢንዱስትሪ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከተጣሉ ባትሪዎች÷ የኒኬል፣ ኮባልት እና ሊቲየም ይዘቶችን በጥራት በመለየት ዳግም ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል፡፡
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከአንድ የተጣለ ባትሪ እስከ 95 በመቶ የኒኬል እና የኮባልት ይዘት መልሶ ማግኘት ሲቻል እንደ ጣቢያዎቹ ዘመናዊነት እና አቅም ከ70 እስከ 90 በመቶ ሊቲየም ከአንድ ባትሪ መልሶ ማግኘት እንደሚቻልም ተመልክቷል፡፡
ከፈረንጆቹ 2021 ወዲህ የተጣሉ ባትሪዎችን ከአቅራቢዎች በአነስተኛ ዋጋ በመረከብ ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ መቻሉን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል፡፡
ቻይና በፈረንጆቹ 2022 ላይ 277 ሺህ ቶን ያህል ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ ባትሪዎችን ከአቅራቢዎች በአነስተኛ ዋጋ በመግዛት አድሳ ጥቅም ላይ ማዋሏ ተነግሯል፡፡
በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሥድስት ወራት ብቻ እንኳ 115 ሺህ ቶን ባትሪ ሰብስባ በማደስ ጥቅም ላይ ማዋሏን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡
እስከ ፈረንጆቹ 2025 በዓመት 1 ሚሊየን ቶን ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ ባትሪዎችን በዓመት ለመሰብሰብ መታቀዱም ተገልጿል፡፡
ቻይና ካገለገሉ ባትሪዎች መልሳ ማግኘት የምትችላቸውን ሐብቶች በጥራት በመለየት ረገድ ቴክኖሎጂዎቿን እያሻሻለች መሆኑን የኢንዱስትሪ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምክትል ሚኒስትር ዢን ጎቢን ተናግረዋል፡፡