አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ2016 በጀት ከ8 ነጥብ አራት ቢሊየን ብር ሆኖ በምክር ቤቱ ጸደቀ፡፡
ምክር ቤቱ ለ2016 በጀት አመት የቀረበውን 8 ቢሊየን 432 ሚሊየን 778 ሺህ 500 ብር የክልሉን በጀት ነው መርምሮ በሙሉ ድምጽ ያፀደቀው፡፡
ለክልሉ ከተያዘው በጀት ውስጥ 3 ቢሊየን 630 ሚሊየን 655 ሺህ 184 ብሩ ከፌዴራል መንግስት በድጎማ የሚገኝ መሆኑ ተገልጿል።
3 ቢሊየን 562 ሚሊየን 282 ሺህ 452 ብር ደግሞ በክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ የሚሸፈን ሲሆን÷ ቀሪው ደግሞ ከተለያዩ የገቢ አማራጮች የሚገኝ መሆኑን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ገልጿል፡፡
የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን÷ በበጀት ዓመቱ የተያዘውን በጀት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በየደረጃው ክትትል ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
በተለይም ነባር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ቅድሚያ ይሰጣል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ከበጀት አቅሙ ጋር በተጣጣመ መንገድ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑም ተገልጿል፡፡
የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችን በወቅቱ ለመመለስ በክልሉ ያሉትን ለገቢ የሚሆን ምቹ አቅሞች በመጠቀም የሚሰበሰበውን ገቢ እያሳደጉ መሄድ እንደሚጠበቅ አቶ አሻድሊ ሀሰን አሳስበዋል።