የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከ1 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መሠራታቸው ተመለከተ

By ዮሐንስ ደርበው

July 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ከ1 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የሕብረተሰብ ተሳትፎ ካውንስል የ2015 ዓ.ም ማጠቃለያ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።

የካውንስሉ ሰብሳቢ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት÷ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በገንዘብ የማይተመኑ እና ሚናቸውም የጎላ ነው፡፡

መንግስት የማስተባበር ሚናን በሚወስድባቸውና ሕብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ በአደረገባቸው ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በብሎክ ተደራጅቶ በየሰፈሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ጠግኗል ብለዋል፡፡

የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ረገድም አዲስ አበባ ሰላማዊ ከተማ እንድትሆን የማይተካ ሚና ተጫውቷል ማለታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመትም÷ መንግስት ያቀዳቸው እና እየሰራቸው ያሉ ሽራዎች የሕብረተሰቡን የነቃ ተሳትፎ እንደሚፈልጉ አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም በትምህርት ለትውልድ፣ በክረምት በጎፈቃድ፣ በአረጋውያን የቤት እድሳት፣ በሕጻናት መጫወቻና መዝናኛ እንዲሁም በአረንጓዴ ዐሻራ ከሕብረተሰቡ የጎላ ተሳትፎ ይጠበቃልም ብለዋል።