አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ (ናም) አባላት ስብሰባን በኢንተርኔት ተሳትፈዋል።
ስብሰባው “ኮቪድ19ኝን በአንድነት መግታት” በሚል ርዕሰ የተዘጋጀ መሆኑን በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ ንቅናቄውን ከመሠረቱ 25 ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን፥ ከ1947 ጀምሮ ንቁ ተሳታፊ ሆና ቀጥላለች።
ከስብሰባው ዐበይት ውጤቶች መካከል ኮቪድ19 ያስከተለውን ሉላዊ ቀውስ ለመከላከል በአባል ሀገራቱ መካከል የዓለም አቀፍ ትብብርን ዕሴት ማጠናከር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በስብሰባው ወቅት ኮቪድ19 በዓለም አቀፍ ደረጃ ባስከተለው ጫና እንዲሁም በተወሰዱ የመከላከል እርምጃዎች ላይ ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም የጋራ ደኅንነትን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መነሣት እንደሚገባ በዚህ ወቅት ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም አፋጣኝ ዓለም አቀፍ ትብብር እና አመራር እንደሚያስፈልግ፣ ኢኮኖሚን እና የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ከድቀት መታደግ ስለሚቻልበት እና እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ አካላት የምግብ ዋስትናን ስለ ማረጋገጥ እንዲሁም ዕዳ ስረዛን ተፈጻሚ ለማድረግ ጥረት ማድረግ የሚቻልበትን አግባብ በተመለከተ ሃሳቦችን አንስተዋል።
በእነዚህ አቅጣጫዎች በትብብር ጥረት ማድረግ ከተቻለም ያለ ጥርጥር ፈተናውን በአሸናፊነት ማለፍ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።