ቢዝነስ

ደቡብ ክልል ከቱሪዝም ዘርፉ 271 ሚሊየን ብር ገቢ አገኘ

By ዮሐንስ ደርበው

July 23, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2015 (2015) በ2015 በጀት ዓመት ከቱሪዝም ዘርፉ 350 ሚሊየን ብር ለማግኘት አቅዶ 271 ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን የደቡብ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ።

ከ4 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ክልሉን መጎብኘታቸውን የቢሮው ምክትል እና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ ፍሬሕይወት ዱባለ ገልፀዋል።

5 ነጥብ 5 ሚሊየን ጎብኚዎች ክልሉን እንደሚጎበኙ ቢታቀድም መፈፀም የተቻለው 81 በመቶ ነው ብለዋል።

20 ሺህ የውጭ ዜጎች ክልሉን እንደሚጎበኙ ታቅዶ የጎበኙት 10 ሺህ 200 መሆናቸውንም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

አጠቃላይ ገቢውም ከአለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ59 ሚሊየን ብር ቅናሽ አሳይቷል ነው ያሉት።

በዘርፉ ለ65 ሺህ ወገኖች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፥ 38 ሺህ 58 የሥራ ዕድል ብቻ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ለዕቅዶቹ ሙሉ በሙሉ አለመፈፀም የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን በምክንያትነት አቅርበዋል።

በዮሐንስ ደርበው