አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ከመከሰቱ በተጨማሪ በየአካባቢዎቹ የታየው የፍትሃዊ ክፍፍል ችግር ተጨማሪ ጫና ማሳደሩ ተገለጸ፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ወቅታዊ የግብርና ስራዎችን አስመልክቶ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በባህር ዳር ዛሬ አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ በክረምት ወራት የግብርና ሥራዎች ተገምግመዋል፡፡
በመድረኩ የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) ÷ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የተፈጠረው ችግር በግብርናው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ከመከሰቱ በተጨማሪ በየአካባቢዎቹ የታየው የፍትሃዊ ክፍፍል ችግር ተጨማሪ ጫና ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማም በግብዓት ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት በክልሉ በ2015/2016 የመኸር እርሻ ለመሸፈን የታቀደውን 5ሚሊየን ሄክታር ለመሸፈን እንዲቻል ለመምከር መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አብዱ ሁሴን የዞን አስተዳዳሪዎች እና የዘርፉ ባለድርሻዎች ተገኝተዋል፡፡
በለይኩን ዓለም