Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመረቁ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመረቁ።

 

በዚህም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያየ መርሐ ግብር ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመርቀዋል።

 

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 550 ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመርቋል።

 

ዩኒቨርሲቲው የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በመደበኛ እና ተከታታይ መርሐ-ግብር ያሰለጠናቸው ሲሆኑ፥ ተመራቂዎቹ በቋንቋ እና ስነ-ሰብ፣ በትምህርትና ስነ-ባህሪ፣ በተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በስፖርት አካዳሚ የትምህርት ክፍሎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸው ተጠቁሟል።

 

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲም ቱሉ አወሊያ ዋናው ግብ በተለያዮ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 521 ተማሪዎች ያስመረቀ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 177 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።

 

በተመሳሳይ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡

 

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት  ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የተመራቂ ተማሪ ወላጆች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

 

እንዲሁም ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምርት ክፍሎች አሰልጥኖ በመጀመሪያ ዲግሪ 3 ሺህ 896፣ በሁለተኛ ዲግሪ 796፣ በዶክትሬት ዲግሪ 65 እንዲሁም በጤና ስፔሻሊቲ 22 ተማሪዎችን አስመርቋል።

 

ከተመረቁት ተማሪዎች በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከመቀሌና አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ 145 ተማሪዎች ይገኙበታል።

 

እንዲሁም ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ10 የትምህርት ፕሮግራሞች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦሥተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸ 2 ሺህ 377 ተማሪዎች ለምረቃ በቅተዋል።

 

እንዲሁም አርሲ እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሠለጠኗቸውን ተማሪዎች አስመርቀዋል።

 

በከድር መሀመድ፣ በተሾመ ኃይሉ ተጨማሪ መረጃ ከኢዜአ እና አሚኮ

Exit mobile version