አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የተፈጠረው ችግር በግብርናው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኃይለማርያም ከፋለ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የክረምት ወቅታዊ የግብርና ስራዎችን በተመለከተ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ በክረምት ወራት የግብርና ሥራዎች እየተገመገሙ ይገኛል።
በመድረኩ የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፋለ÷ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የተፈጠረው ችግር በግብርናው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ከመከሰቱ በተጨማሪ በየአካባቢዎቹ የታየው የፍትሃዊ ክፍፍል ችግርም ጫና አሳድሯል ብለዋል።
የመድረኩ ዓላማም በግብአት ላይ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት በክልሉ በ2015/16 የታቀደውን 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመኸር እርሻ ለመሸፈን እንዲቻል ለመምከር መሆኑ ተነግሯል።
በመድረኩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱ ሁሴን የዞን አስተዳዳሪዎች እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በለይኩን አለም