አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና እና ሩሲያ ጥምር የባሕር እና የአየር ኃይል የጦር ልምምድ በጃፓን ባሕር ላይ መጀመራቸው ተነገረ።
የ”ሰሜኑ ወይም መስተጋብር 2023″ የተሰኘው የሁለቱ ሀገራት የጦር ልምምድ ከዓመታዊ የትብብር ዕቅዳቸው ጋር የተጣጣመ መርሐ-ግብር መሆኑን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
የልምምዱ መሪ-ሐሳብ “ስትራቴጂያዊ የባሕር ሰርጦችን ደኅንነት መጠበቅ” የሚል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዓላማውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂያዊ ቅንጅት ማጠናከር ፣ የአካባቢውን ሠላም እና መረጋጋት ማስፈን ፣ ያላቸውን የጋራ አቅም ማጠናከር እና ለደኅንነት ችግሮች ውጤታማ እና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት መሆኑን የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጥምር ጦር ልምምዱ 10 መርከቦች እና 30 የጦር አውሮፕላኖች ተሳትፈዋል ተብሏል።
ቻይና እና ሩሲያ በባሕር እና በአየር መከላከል እና ማጥቃት ላይ ያተኮረ ልምምድ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት ይሠራሉ ተብሏል፡፡