Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሲስተር ወርቅነሽ ኬሬታ እና ሲስተር መስከረም ሰጠኝ የ2023 የጤናው ዘርፍ ጀግኖች ተባሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ“ውሜን ኢን ግሎባል ኸልዝ” በተዘጋጀው የ2023 የጤናው ዘርፍ ጀግኖች የሽልማት መርሐ – ግብር ሲስተር ወርቅነሽ ኬሬታ እና ሲስተር መስከረም ሰጠኝ የ2023 የጤናው ዘርፍ ጀግኖችን ሽልማት አሸነፉ፡፡

በርዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ በተዘጋጀው የ“ውሜን ኢን ግሎባል ኸልዝ” መርሐ-ግብር ከእያንዳንዱ የዓለም ክፍል ለ65 የጤናው ዘርፍ መሪዎች የጤናው ዘርፍ ጀግኖች በሚል እውቅና ሰጥቷል።

በአቻዎቻቸው ዘንድ “የወጣቶች እናት” የሚል ቅፅል ሥም ያተረፉት ሲስተር ወርቅነሽ ከሬታ አብሺሮ የ2023 የጤናው ዘርፍ ጀግና እውቅና ካገኙ ሴቶች መካከል አንዷ ኢትዮጵያዊት ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ሲስተር መስከረም ሰጠኝም ÷ በሙያቸው በጤናው ዘርፍ አዋላጅ ነርስ ሲሆኑ እውቅናውን ያገኙት ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ለመሆን በቅተዋል፡፡

ሲስተር መስከረም ሰጠኝ በጤናው ዘርፍ በሚሠሩት የአቅም ግንባታ ሥራ ከዲስትሪክት ጤና ቢሮዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ ሲሆን፥ በሴቶችና ወጣቶች የሥርዓተ-ፆታ አገልግሎቶችን እና የጤናው ዘርፍ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚሰሩት ሥራ ይታወቃሉ፡፡

በሴቶች እና ወጣቶች ላይ ከሚሰሩ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበርም ወጣቶችን ማብቃት ላይ በሰሩት ሥራ የዕውቅናው አሸናፊ ሆነዋል።

ሲስተር መስከረም ሰጠኝ ከ“ፓካርድ ፋውንዴሽን” በቅርቡ የ2022 የጥራት ፈጠራ ፈተና ሸልማትም አግኝተዋል፡፡

በስራ ጓዶቻቸው ዘንድ “የወጣቶች እናት” የሚል ቅፅል ሥም የተሰጣቸው ሲስተር ወርቅነሽ ኬሬታ አብሺሮ ‘የ2023 የጤናው ዘርፍ ጀግና’ የሚል ዕውቅና በ“ፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ” ተሰጥቷቸዋል።

ሲስተር ወርቅነሽ የኢትዮጵያን የኅብረተሰብ ጤና ማኅበር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆንም የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እና ወጣቶች የሥርዓተ-ፆታ እና ሥነ-ተዋልዶ ላይ ረጅም ጊዜ የሰሩ ብርቱ ሴት መሆናቸውን የፓዝ ፋይንደር መረጃ ያመላክታል፡፡

በነርስነት ሙያቸው በገጠር አካባቢ ስራ በጀመሩበት ጊዜ በነበረው የሰው ሃይል እጥረት ምክንያት አዋላጅ ነርስም የፋርማሲ ባለሙያም በመሆን አገልግሎት ሰጥተዋል።

ሲስተር ወርቅነሽ “ፓዝፋይንደር ኢትዮጵያ” የተሠኘውን በጤናው ዘርፍ የሚሠራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከተቀላቀሉ በኋላ በሞዛምቢክ ሥልጠና በመውሰድ በጤናው ዘርፍ ከወጣቶች ጋር የሚስማማ መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ ለመቅረጽ በቅተዋል።

በዓለማየሁ ገረመው

Exit mobile version